Friday, June 27, 2014

የቱ ይቀድማል ?

ኢትዮጵያዊነት ፣ ብሔር እና ሰው መሆን 
 ብዙ ግዜ ብሔርተኝነትንም ይሁን ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ ግለሰቦች  አንድን ነገር ሲዘነጉ ይስተዋላል፡ በዚህም የተነሳ አብዛኛውን ማህበረሰብ ግራ ያጋቡታል። 
ነገር ግን ሁሉም ሊያስታውሰው እና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ ሰው መሆንን ነው።
እንደኔ እምነት ሁለቱም ወገኖች የራሳቸው እውነት አላቸው 
በየራሳቸው መንገድ ትክክልም ናቸው ስለዚህ ሁለት ትክክል የሆኑ ነገሮችን እንደ ተቃራኒና ተፃራሪ ነገር ከማየት ይልቅ የሚታረቁበትን መንገድ መገንዘብ ተገቢ ነው   ይህም ሰው መሆን ነው ማንም ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያረገ መስሎት ብሔሮችን ካላከበረ ፣ብሔሮች ራሳቸውን ከፍ ያረጉ መስሏቸው የሌላውን ብሔር ግለሰብ ካዋረዱ ሁሉም ከንቱ ነው። እውነታው ይህ ነውና አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ቢወደው ሙሉ ማንነቱን መቀበል አይከብደውም ብሔሩን ፣ ቋንቋውና ባሕሉን ያከብርለታል ፡አንዱ ያንዱን ብሔር ፣ ቋንቋና ባሕል ካከበረ በአድነቱ ማሰሪያ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ማሕበረሰብ ይፈጠራል።
ያኔ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው ብለን በሙሉ ልብ ቀና እንላለን



ቅደም ተከተሉም ይህ ነው
ሰው
ብሔር
ኢትዮጵያ



Tuesday, April 8, 2014

የቅኔ አዝመራ

የቅኔ አዝመራ 

# መመሳሰል # 

ግርማ ሞገሥ አለህ
 ጦብያና ግብጥን ባንዴ ትረግጣለህ 
እውነትም አባይ ነህ 


  ¤    ¤    ¤    ¤  ¤    ¤    ¤   ¤


* ቅናት * 

ክፋት ምቀኝነት ሥራችን ሆነና
 ልጁ በተማረ ቤተ-ዘመድ ቀና


 ¤    ¤    ¤   ¤   ¤    ¤    ¤   ¤


 > ምርጫ < 

ቁመናና ዛላሽ እጅጉን ድንቅ ነው
 ውበት ደም ግባትሽ የማይታበል ነው
 ችግርሽ ከወዲህ ካለባበስሽ ነው
 ዓሣ ጉርድ በሸሚዝ
 ሲሻሽ ሙሉ ቀሚስ 
ቲሸርት ቃሪያ ሱሪ 
ለብሰሽ ብትኩራሪ 
ሁሉ ያምርብሻል 
ግና ያልለመድሽው ድሪያ አበላሽቶሻል 

  ¤    ¤    ¤   ¤  ¤    ¤    ¤   ¤ 
 
      yitesam ዘ - ሐረር

Friday, March 14, 2014

አምሣለ ዮርዳኖስ


ስለ ፍቅር ብዬ
 ሁሉን ነገር ችዬ 
ባበዛ ዝምታ 
ንቀቱ በረታ
 ንፁህ ልቤን ወግቶ 
ውስጠቴን አድምቶ 
ጥሎኝ ከመንገዱ 
ጊዚያት ነጎዱ
 በጥላቻው ጥልቀት
 በበደሉም ር'ቀት
 ዓይኔ እንባ አፈለቀ
 አካሌን ጠመቀ
 ሠው በሚሉት ካህን 
ዙሪያውን ሲታጠን 
 ገብቼ ከወንዙ ሕይወት ከሚሉቱ 
ዕንባ ሆኖኝ ጠበል ተነከርኩኝ ውሥጡ
 ጠልቄ ብወጣ 
አዲስ ፀሐይ ወጣ 
 ዛሬ እኔም ተካንኩ
 ደግነትን ጣልኩ 
 ሥለ ሠው-ልጅ ክፋት ውሥጤ ተሠበረ
 እርኩሠት ተረጨ ክፋትን ዘመረ

 yitesam ዘ- ሐረር