ባጨለሙት ሰማይ
በገዙት ምድር ላይ
የክፋት ዘር ዘርተው
አንዱን ሐረግ ባንዱ እየጠመዘዙ
ዘመናት ተጓዙ
የቀመሩት ቀመር
የሸረቡት ሴራ ድንግዝግዝ ፈጠረ
አንዱ ግንድ ከሌላው ፍትጊያ ጀመረ
ሐገር ጽልመት ዋጣት
ጨለማ ነገሰ
ሌባው ተመችቶት የልቡ ደረሰ
ጨለማ ነው ብሎ እንዳሻው ሲጋልብ
ያሻውን ሲያደርግ
አንዱ አንዱን እንዲጥል ሲያፋትግ ሲያፋትግ
ከፍትጊያው መሃል እሳት ብልጭ አለ
ብርሃን ፈነጠቀ
እውነተኛው ጠላት ተለየ ታወቀ
በደም መስተፋቅር ሐረግ ተዋደደ
አንድነት ነገሰ ሰላም ተወለደ
የነፃነት ፋና ጮራ ፈነጠቀ
ሰውነት ከበረ ሰውነት ደመቀ
No comments:
Post a Comment