Wednesday, May 23, 2018

አምባ ልውጣ!

መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!

አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት ፤ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፤ ልገላገል ከህመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፤ ደጋግሜ፤ ማህሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፤እርቃኔን ከሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ እሚነደውን፤ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፤ ውዳሴዋን ደጋግሜ...
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፤ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፤ ነጋ፤ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፤ አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፤ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!

                          ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድሀን፣ እሳት ወይ አበባ!

Tuesday, May 8, 2018

እንደሥራው

እግር አንፈራጦ
እጅ አጥፎ ተቀምጦ
ከቶ ምን ሊመጣ ምን ከምን ተገኝቶ
አውጣኝ ያለ ወጣ አብላኝ ያለም በላ
ተኝቶ የዋለ አሳማ ተበላ
ቢሆንም ብሂሉ
ወዲ እኮ ነው ቅሉ
አብላኝ ያለ አንበሳ
ለአደን ተነሳ
ጫካውን አሰሰ
የድካሙን ዋጋ ፍሬውን አፈሰ
አውጣኝ ያለ ፈረስ
ጠላት ከሱ እንዳይደረስ
ሮጠ ፈረጠጠ
በጠንካራ እግሮቹ
ከመጣበት መቅሰፍት ጥፋት አመለጠ
ስንፍና ተጭኖት የተኛው አሳማ
የጠላትን መድረስ በፍፁም ሳይሰማ
ሩቅ እንደተመኘ እሩቅ እንዳለመ
ጥቂት ሳይራመድ በሞት ተቀደመ
እናም
ይህ ነው ሕይወት ቅሉ
እሩጡ ውጡ እንጂ አውጣን አትበሉ
Samson mekonnen

ላሜ

ያኔ በዝቶ ግቷ
ምን ቢሞላ ጡቷ
ጊዜ በመጥፋቱ
ባከነ ወተቱ
ዛሬ ግዜ አግኝቼ
ማለቢያ አንግቼ
እምቢ አለኝ ወተቷ
ነጥፋለች ላሚቷ
አወይ ጥበብ ከንቱ
አወይ ብዕር ከንቱ
በጊዜው ካልያዙት ያሳዝናል ሞቱ።
ሳምሶን መኮንን

ጨረቃ ና ናፍቆት


እቱ የጥንቲቱ
የጥርስሽ ንጣቱ 
የጉንጭሽ ቅላቱ 
ውል ይለኛል ዛሬም የገላሽ ሙቀቱ 
የእግሮችሽ ኮሽታ 
የፍቅርሽ ሹክሹክታ 
ያ የሣቅሽ ዜማ የበዛው ክትክታ 
ይሠማኛል ዛሬም ናፍቆት ሲበረታ
እቱ የጥንቲቱ 
አንቺም ትዝ ካለሽ ካለብሽ ናፍቆቱ 
ይህ ነው መዳኒቱ 
ባስለመድኩሽ ሰዓት ባለሽበት ቦታ 
ቀና በይ ላንድ አፍታ
እኔም ባለሁበት ባስለመድሽኝ ሰዓት
ዓይኖቼን አቅንቼ
ጨረቃን አይቼ  ልግባ ተፅናንቼ 
አንቺም በዚያች አፍታ 
ጨረቃዋን ፈክታ 
ካየሻት ተጽናኚ 
በይ ቃሌን እመኚ 
ምንም ብንራራቅ ካንድ ሰማይ ሥር ነን
  ነገ አብረን ለመኖር ታላቅ ተሥፋ አለን

Saturday, May 5, 2018

እንቆቅልሽ

እንቆቅልሽ
አንድ ሰው ተራበ
እጆቹን ታጠበ
መዓድ አቀረበ
የገበታው ዓይነት መዓዛው ቢያውድም
ለተራበ ስጋው ያቀረበው ሁሉ ምን በቂ ቢሆንም
ዕትኡ በሰላም እስኪባል አልበላም
እንቆቅልሽ
ሌላውም ተርቦ
እጆቹን ተጣጥቦ
ማዕዱን አቅርቦ
ካማረ ገበታው ካረደው ፍሪዳ ከጠላ ከጠጁ
ሊጠጣ ሊበላ ቢዘረጋም እጁ
ፍላጎት ግን ከዳው
በድኑን አስቀምጦ መንፈሱ ግዜ አጣ ሐሳብ
አነጎድው
እንቆቅልሽ
አንድም ከዚ አለ
ተርቦ የዋለ
ምን ርሃብ ቢሰማው ቢጨማደድ ፊቱ
ምን  ቢጮህም ወስፋቱ
እጁን አይታጠብ
ማዕዱን አያቀርብ
ጥግ ይዞ ተቀምጧል
በደከሙ  ዓይኖቹ ህዝቡን ያማትራል
እንቆቅልሽ
አማኝ ነብሱን ብሎ
ሐብታሙ ሲጨነቅ
ድሃው ግን በማጣት
ሶስት ሰወች ተራቡ  ዓለም እንደዚ ናት
እንቆቅልሽ ህይወት እንቆቅልሽ ዓለም
ከጥያቄ በቀር ምን ጊዜም መልስ የለም!!!!!!!