እቱ የጥንቲቱ
የጥርስሽ ንጣቱ
የጉንጭሽ ቅላቱ
ውል ይለኛል ዛሬም የገላሽ ሙቀቱ
የእግሮችሽ ኮሽታ
የፍቅርሽ ሹክሹክታ
ያ የሣቅሽ ዜማ የበዛው ክትክታ
ይሠማኛል ዛሬም ናፍቆት ሲበረታ
እቱ የጥንቲቱ
አንቺም ትዝ ካለሽ ካለብሽ ናፍቆቱ
ይህ ነው መዳኒቱ
ባስለመድኩሽ ሰዓት ባለሽበት ቦታ
ቀና በይ ላንድ አፍታ
እኔም ባለሁበት ባስለመድሽኝ ሰዓት
ዓይኖቼን አቅንቼ
ጨረቃን አይቼ ልግባ ተፅናንቼ
አንቺም በዚያች አፍታ
ጨረቃዋን ፈክታ
ካየሻት ተጽናኚ
በይ ቃሌን እመኚ
ምንም ብንራራቅ ካንድ ሰማይ ሥር ነን
ነገ አብረን ለመኖር ታላቅ ተሥፋ አለን
No comments:
Post a Comment