Sunday, July 29, 2018

የፍቅር ጮራ

ባጨለሙት ሰማይ
በገዙት ምድር ላይ
የክፋት ዘር ዘርተው
አንዱን ሐረግ ባንዱ እየጠመዘዙ
                          ዘመናት ተጓዙ
የቀመሩት ቀመር
የሸረቡት ሴራ ድንግዝግዝ ፈጠረ
አንዱ ግንድ ከሌላው ፍትጊያ ጀመረ
ሐገር ጽልመት ዋጣት
ጨለማ ነገሰ
ሌባው ተመችቶት የልቡ ደረሰ

ጨለማ ነው ብሎ እንዳሻው ሲጋልብ
ያሻውን ሲያደርግ
አንዱ አንዱን እንዲጥል ሲያፋትግ ሲያፋትግ

ከፍትጊያው መሃል እሳት ብልጭ አለ
ብርሃን ፈነጠቀ
እውነተኛው ጠላት ተለየ ታወቀ
በደም መስተፋቅር ሐረግ ተዋደደ
አንድነት ነገሰ ሰላም ተወለደ
የነፃነት ፋና ጮራ ፈነጠቀ
ሰውነት ከበረ ሰውነት ደመቀ

Friday, July 13, 2018

ኩኩ መለኮቴ

            ( ጉጉ)  ኩኩ መለኮቴ
ፍርድ ተበደለ
ፍትህ ተጓደለ
አቤቱታ ሰሚ ቅን ፈራጅ ሰው ጠፋ
አህያው እያለ ዳውላው ተገፋ

ኩኩ መለኮቴ የብሶት ጩኸቴ
ፍርድ መማጸኛ በልጅ አንደበቴ
ዛሬ ሰሚን ቢያገኝ ላዚመው በርጅና
ካንቀላፉት መሃል ንቁ አይጠፋምና

ኩኩ ኩኩ ኩኩ
ኩኩ መለኮቴ
ጉርሻ ያነቀው ሰው
ዳግም አይበላም ወይ ?
ንገሩኝ በሞቴ

ያድነኛል ያለው መድሃኒት ቢያቆስለው
ባንድነት ፈርጆ
መድሃኒት ሁሉ መርዝ ብሎ ይላል ውይ ሰው?

ኩኩ ኩኩ ኩኩ
ኩኩ መለኮቴ
እሷ "ባጠፋችው"
በኔ ላከከችው

Tuesday, July 3, 2018

ያንተ ስፌት

ያንተ ስፌት

ለኔ ያልኩት ሁሉ
አንዳንዱ እየሰፋ
ሌላ እየጠበበኝ
የሚሆነኝ ጠፍቶ
ይኸው ራቆቴን ነኝ
……………………………………
ልክ ማውቅ መስሎኝ
ምኞት ተከትዬ
ያንተን መልካም ፈቃድ
በስሜቴ ጥዬ
ይኸው አሁን ድረስ
ብቀድም ብሰፋ
ከዚህ ሁላ ምኞት
የሚሆነኝ ጠፋ
………………………………
ስለዚህ አባቴ
ፍቃድህ እውነት ነው
አንተው ጨርስልኝ
የኔ ምኞት ረዝሟል
ባንተ መልካም ፈቃድ
በልኬ ስፋልኝ

                  ከልዑል ሀይሌ
@getem
@getem
@lula_al_greeko

ፍቅር ያሸንፋል!!!!!

ሳያውቁ በስህተት.......
የ 28 ዓመታቱ አገዛዝ በጣም በሚገርም ሁኔታ ድምጽ አልባ አቢዮት ተካሂዶበት የተገለበጠና ያበቃለት ይመስላል።
በደም የተገኘ ስልጣን በደም ካልሆነ ከእጅ አይወጣም የሚለውን መፈክር ያፈረሰ ታላቅ ትግል ታላቅ ድል ይዞ መጥቷል ።
ነገር ግን በነዚያ ሁሉ ጊዜያት የተዘራው መርዝ በ አንዲት ጀንበር ይጠራል ማለት ባይቻልም የሚጠበቅ ጥቂት ለውጥ ግን መታየት አለበት።

በርግጥ ይህ ጥቂት ብዬ ያስቀመጥኩት ለውጥ ታላቅና ለሐገራችን ህልውና እና ለምንጠብቀው እድገት ወሳኝ መሰረት ነው።
ታዲያ ለምን ጥቂት ለውጥ አልክ ካላቹኝ ግን ምክንያቱም ይህ ለውጥ በዶክተር አብይ አህመድ እና በአመራራቸው ሊመጣ ስለማይችልና ይልቁንም ከያንዳዳችን ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች የሚጠበቅ በመሆኑ ነው።

ይህ ለውጥ ምንድነው? ካልን ደግሞ ከዘረኝነት የፀዳ! አመለካከትን ማዳበር ነው።
ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ መንገዱን አሳይተውናል በዘር መርጠው ሳይሆን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ወደው አንድነትና ፍቅርን ሰብከዋል ።

ይህን ጥሪ አለመቀበል ግን ሳያውቁ በስህተት  የነበረውን አፋኝ አገዛዝ እሳቤ ማራመድ ነው
ምክንያቱም ዓላማቸው አንድ እና አንድ የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘርና በሐይማኖት እያጋጩ የስልጣን ጊዜን ማራዘምና ወንበራቸው ከተገፋ ህዝቡን ማጫረስ ስለሆነ።

ደስ የሚለው ግን ስልጣናቸው አብቅቷል ሕዝቡም አንድነትን መርጧል በዚ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ  ያለፈበትን ሀሳብ ለማራመድ ዘር እየጠቀሱ መሳደብና ልዩነትን ለመፍጠር መሞከር ያስገርማል ይህን የምታደርጉ ሰዎች ሳታውቁት ከሆነ ስህተት መሆኑን ተረዱ ሆን ብላቹ ከሆነ ግን ህዝብ አንድነትን መርጧልና አትልፉ ነን ብላቹ የምትለጥፉትንም ብሄር አታውቁትም አትወክሉትምም!!!!

Wednesday, June 27, 2018

ዳማ

ንጉስ ያደርጉሃል
                    ሲሻቸው ወታደር
እግዜርና ሰይጣን ዳማ ሲጫወቱ
               አንተን አርገው ጠጠር
                    
               ሜሮን ጌትነት "ዙረት"

Monday, June 25, 2018

✍✍ግስ✍✍

           ✍✍ግስ✍✍
ሀ ን ከበ የለዪ ፊደል የቆጠሩ
አንድ ዓረፍተ ነገር ፈልገው ሊሰሩ
ሐገራችን ድሃ። ብለው ተናገሩ

ስህተታቸው ነዶኝ
ነገሩ ከንክኖኝ ታይቶኝ ግድፈታቸው 
ቢታረሙ ብዬ ግስ አከልኩላቸው
ሐገራችን ድሃ ትነሳለች። ብዬ
ሐገራችን ይኸው ድሃ ቆመች። ብዬ

✍✍✍@1999 ✍✍✍

Saturday, June 23, 2018

🌙☀🌞 ይነጋል 🌞☀🌙

                   🌙☀🌞ይነጋል

ደማቂቱ ፀሐይ ከዓይን ተሰውራ ሰማዩ ቢዳምን

ምድር ጭጋግ ለብሳ የድቅድቅ ጨለማ      ጽልመቱ ቢውጠን

ሂደቷ ነውና የማይለዋወጥ የጊዜ ቀመሯ

እንደመሸ አይቀርም ይነጋል ይታያል የብርሃን ጮራ 🌞
✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍✍

ብላቴናው እና ሙሴ

ያለግዜው የተዘመረ !!!
      ብላቴናው እና ሙሴ

ቴዲ አፍሮ ዘመን በማይሽረው ዜማ ያልገባቸውና ከህሊናቸው መታረቅ ያቃታቸው እንደሚሉት "ቁጣና አመጽ " ሳይሆን  ፍቅርና ተግሳጽ ያዘለ ምክርን  ጃ ያስተሰርያል ሲል
ህዝብ ልብ ከገባ እነሆ 13 ዓመታት ።
በግዜው ስልጣን ላይ የነበሩት ሰወች የመጡበትን ዓላማና ያለፉበትን መንገድ ረስተው ህዝብን ሲያስጨንቁና ሲያሸብሩ ህዝብም ልዪነቱ ውበት እንጂ መጥፊያው እንዳልሆነ በማመን በአንድነት "በመደመር"  በሕብረትና በቅንጅት ሆ ብሎ የወጣበት ብዙ እልቂትም የነበረበት መሆኑ አይረሳም።
ብላቴናው ያኔ
በ17 መርፌ በጠቀመው ቁምጣ
ፀጉሩን ያጎፈረው ዙፋን ላይ ሲወጣ
እንዳምናው ባለቀን ያምናውን ከቀጣ
አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ
ሲል ድምፁን ከፍ አደረገ
ብዙወች ይሄን ቃል እንደ ስድብ ያዩታል ነገር ግን ስድብ አይደለም ለ17 አመት ልብሳቸው በላያቸው እስኪያልቅ ለነፃነት የታገሉ ሰወች ዓላማቸውን ረስተው እንደ ቀድሞው አፋኝ ስለሆኑ እንዲነቁ ነበር ጥሪው
ለዛም ነው መደምደሚያው
ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ
ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ
  ጃ ያስተሰርያል
የሆነው
ይህ ብቻም አይደለም ብላቴናው
ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ
ኧረ አይበቃም ወይ  ኢትዮጵያዬ
ብሎ ሲፀልይና እጁን ወደላይ ሲያነሳ
ፈጣሪ የሕዝቡን እንባ አይቶ እንደሚመልስ በቃ ብሎ ያን የተመኘውን ሰላምና እርቅ እንደሚያመጣ አንድነታችንም እንደሚመለስ
ሙሉ እምነት ነበረው ለዚህም ነበር አሳይተው የነሱንን እርቅና ሰላም ባየ ጊዜ
አበባ አየሽ ወይ? ለምለም
አበባ አየህ ወይ? ለምለም
ብሎ ያዜመው
ዳግም ተጠምዝዘው ሰላሙን ባያደፈርሱት
የብላቴናው ዝማሬ  ዘመኑን ጀመርነው ይኸው ታርቀን -------ለዓለም እንዳይለያየን ዘለዓለም  ብሎ ማዜሙ ምነኛ ያማረ ነበር ? ነገር ግን ቢዘገይ እንጂ አልቀረምና ያ ያለግዜው የተዜመው ዜማ አሁን ላይ ከፍ ተደርጎ ይከፈት አበባ አየህ ወይ?  አዎ እኔ አይቻለው ያውም ለምለም!!!!
አሁን የብላቴናው ፀሎት ተሰምቷል
 
ዘ-ፀሃት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ
ባህሩን ሚያሻግር አንድ ሙሴን ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳኤ
ባንድነት ከገባን የፍቅር ሱባኤ 


     

ዶክተር አብይ  የፀሎታችን ፍጻሜ እንዲሆንና  ኢትዮጵያችንን ይዞ እንደሙሴ  ወደፊት የሚሻገርበት ዘመን እንዲሆን ተመኘሁ 


    እናንትስ ?  አበባ አየህ ወይ ?
                      አበባ አየሽ ወይ?

የዳህላኩም ህልማችን እውን ይሆናል ገና !!!!!!!!!

Wednesday, May 23, 2018

አምባ ልውጣ!

መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ!

አምባ ወጥቼ እኩለ-ሌት ፤ ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፤ ልገላገል ከህመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፤ ደጋግሜ፤ ማህሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፤እርቃኔን ከሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ እሚነደውን፤ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፤ ውዳሴዋን ደጋግሜ...
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፤ ደሞ ይምጣ የቁም ህልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፤ ነጋ፤ ደፈረሰ ደሜ።
ለሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝ፤ አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፤ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!

                          ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድሀን፣ እሳት ወይ አበባ!

Tuesday, May 8, 2018

እንደሥራው

እግር አንፈራጦ
እጅ አጥፎ ተቀምጦ
ከቶ ምን ሊመጣ ምን ከምን ተገኝቶ
አውጣኝ ያለ ወጣ አብላኝ ያለም በላ
ተኝቶ የዋለ አሳማ ተበላ
ቢሆንም ብሂሉ
ወዲ እኮ ነው ቅሉ
አብላኝ ያለ አንበሳ
ለአደን ተነሳ
ጫካውን አሰሰ
የድካሙን ዋጋ ፍሬውን አፈሰ
አውጣኝ ያለ ፈረስ
ጠላት ከሱ እንዳይደረስ
ሮጠ ፈረጠጠ
በጠንካራ እግሮቹ
ከመጣበት መቅሰፍት ጥፋት አመለጠ
ስንፍና ተጭኖት የተኛው አሳማ
የጠላትን መድረስ በፍፁም ሳይሰማ
ሩቅ እንደተመኘ እሩቅ እንዳለመ
ጥቂት ሳይራመድ በሞት ተቀደመ
እናም
ይህ ነው ሕይወት ቅሉ
እሩጡ ውጡ እንጂ አውጣን አትበሉ
Samson mekonnen

ላሜ

ያኔ በዝቶ ግቷ
ምን ቢሞላ ጡቷ
ጊዜ በመጥፋቱ
ባከነ ወተቱ
ዛሬ ግዜ አግኝቼ
ማለቢያ አንግቼ
እምቢ አለኝ ወተቷ
ነጥፋለች ላሚቷ
አወይ ጥበብ ከንቱ
አወይ ብዕር ከንቱ
በጊዜው ካልያዙት ያሳዝናል ሞቱ።
ሳምሶን መኮንን

ጨረቃ ና ናፍቆት


እቱ የጥንቲቱ
የጥርስሽ ንጣቱ 
የጉንጭሽ ቅላቱ 
ውል ይለኛል ዛሬም የገላሽ ሙቀቱ 
የእግሮችሽ ኮሽታ 
የፍቅርሽ ሹክሹክታ 
ያ የሣቅሽ ዜማ የበዛው ክትክታ 
ይሠማኛል ዛሬም ናፍቆት ሲበረታ
እቱ የጥንቲቱ 
አንቺም ትዝ ካለሽ ካለብሽ ናፍቆቱ 
ይህ ነው መዳኒቱ 
ባስለመድኩሽ ሰዓት ባለሽበት ቦታ 
ቀና በይ ላንድ አፍታ
እኔም ባለሁበት ባስለመድሽኝ ሰዓት
ዓይኖቼን አቅንቼ
ጨረቃን አይቼ  ልግባ ተፅናንቼ 
አንቺም በዚያች አፍታ 
ጨረቃዋን ፈክታ 
ካየሻት ተጽናኚ 
በይ ቃሌን እመኚ 
ምንም ብንራራቅ ካንድ ሰማይ ሥር ነን
  ነገ አብረን ለመኖር ታላቅ ተሥፋ አለን

Saturday, May 5, 2018

እንቆቅልሽ

እንቆቅልሽ
አንድ ሰው ተራበ
እጆቹን ታጠበ
መዓድ አቀረበ
የገበታው ዓይነት መዓዛው ቢያውድም
ለተራበ ስጋው ያቀረበው ሁሉ ምን በቂ ቢሆንም
ዕትኡ በሰላም እስኪባል አልበላም
እንቆቅልሽ
ሌላውም ተርቦ
እጆቹን ተጣጥቦ
ማዕዱን አቅርቦ
ካማረ ገበታው ካረደው ፍሪዳ ከጠላ ከጠጁ
ሊጠጣ ሊበላ ቢዘረጋም እጁ
ፍላጎት ግን ከዳው
በድኑን አስቀምጦ መንፈሱ ግዜ አጣ ሐሳብ
አነጎድው
እንቆቅልሽ
አንድም ከዚ አለ
ተርቦ የዋለ
ምን ርሃብ ቢሰማው ቢጨማደድ ፊቱ
ምን  ቢጮህም ወስፋቱ
እጁን አይታጠብ
ማዕዱን አያቀርብ
ጥግ ይዞ ተቀምጧል
በደከሙ  ዓይኖቹ ህዝቡን ያማትራል
እንቆቅልሽ
አማኝ ነብሱን ብሎ
ሐብታሙ ሲጨነቅ
ድሃው ግን በማጣት
ሶስት ሰወች ተራቡ  ዓለም እንደዚ ናት
እንቆቅልሽ ህይወት እንቆቅልሽ ዓለም
ከጥያቄ በቀር ምን ጊዜም መልስ የለም!!!!!!!